Wednesday, January 27, 2016

የአባይ ፀሃዬ ጦርነት

ከተስፋዬ ገብረአብ (Gadaa)

ከኦሮሚያ አመፅ ጋር በተያያዘ አባይ ፀሃዬ ስሙ በተደጋጋሚ ይነሳል። አንዳንድ ደንፊ ንግግሮች መናገሩንም ስናነብ ሰነባብተናል። ምን እንደነካው እንጃ እንጂ ጠባዩ እንኳ እንዲያ አልነበረም። አባይ በጠባዩ ድመት መሆኑ ነበር የሚታወቀው። ሊያጠቃ ሲፈልግ እንደ ፈረስ ጋማህን እያሻሸ እንጂ እንደ ቋረኛው ካሳ ጎራዴ አያወዛውዝም። ከታላቁ የኦሮሚያ አመፅ ጋር በተያያዘ “በሚናገራቸው ንግግሮች” ግን ስሜቱን መቆጣጠር የተቸገረ ይመስላል። ዞረም ቀረ አባይ ፀሃዬ እና ጓደኞቹ የገጠማቸውን ጦርነት በአሸናፊነት ለመወጣት መጣራቸውን ቀጥለዋል። ይሳካላቸው ይሆን?
በአጤ ሃይለስላሴ ዘመን ገጣሚ ዮፍታሄ ንጉሴ እንዲህ ቋጥሮ ነበር፣
ወላድ ኢትዮጵያ - ምጥ ይዟታል አሉ!
ማርያም! ማርያም! በሉ 
በዚህ ዘመን ኢትዮጵያ በፖለቲካ ምጥ በመያዟ “ማርያም! ማርያም!” እየተባለ ነው። ከመንግስቱ ንዋይ የታህሳስ ግርግር የጀመረው የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምጥ ገና አዋላጅ አላገኘም። እና “ማርያም! ማርያም!” ማለቱ እስከ ዘመናችን ዘልቆአል። በጥንታዊው የኦሮሞ ባህል እናት ልጅ ስትወልድ Bagaa miillikee walqixaate ትባላለች። “እንኳን በእግርሽ (ተስተካክለሽ) ለመቆም አበቃሽ” እንደማለት ነው። በደቡብ ኢትዮጵያ (ወላይታ?) አባባሉ የተለየ ነው። ህፃን ሲወለድ “እንኳን በገባበት ወጣ” ይባላል። እንግዲህ ወያኔ በገባበት እስኪወጣ የኦሮሞ ወጣቶች ትግሉን እንደሚቀጥሉ የቆረጡ ቢሆንም፤ በዚህ መካከል በሚፈጠር አለመተማመን እና ሽኩቻ ምክንያት ግን እድል ተመልሳ ከአባይ ፀሃዬ እጅ ላይ ልትወድቅ ትችላለች።
በቅርቡ የወያኔ ነባር አባል ከሆነ የቀድሞ ወዳጄ ጋር በፅሁፍ ስናወጋ፣
          “የሞጋሳ ዘመዶችህ አይሳካላቸውም። አማሮች ለታክቲክም ቢሆን ከኛ ጋር ናቸው።” አለኝ።

የአባይ ፀሃዬ የፖለቲካ ቁማር በትክክል በዚሁ መንገድ የሚጓዝ ነው። ከዚያ የተሻለ አንዳችም የመቋቋሚያ ዘዴ የላቸውም። በተለይ በአማራ እና በኦሮሞ መካከል አለመተማመኑን በማሳደግ ብቻ በስልጣን የመቆየት እድላቸውን መጨመር ይችላሉ። ከመነሻው በቋንቋ ላይ የተመሰረተ የፌደራል ስርአት ለመጠቀም ሲነሱ በህዝቦች መካከል በሚፈጠር አለመግባባት ስልጣናቸውን ለማቆየት እንደሚችሉ በማመን ነበር። በርግጥም ተጠቅመውበታል። አንዳንድ የዋህ ዜጎች፣ “አዲሳባችን ላይ ወፍ ዝር አይልባትም!” ሲሉ መሰማታቸው የቁማሩ አንድ አካል ነው።

ከኦሮሚያ አመፅ ጋር በተያያዘ ከሳምንታት በፊት ባሌ ሮቤ - መዳወላቡ ዩኒቬርስቲ አንድ አማራ ተማሪ ተገድሎ ነበር። በኦሮሞና በአማራ ተማሪዎች መካከል በተከሰተ አለመግባባት ተማሪው እንደተገደለ ተነግሮም ነበር። የሟቹ ተማሪ አባት ለአሜሪካ ድምፅ ሬድዮ ሲናገር፣

“…ከኦሮሞ ጎረቤቶቻችን ጋር በደስታም ሆነ በሃዘን ጊዜ በፍቅር ተከባብረን ኖረናል። ደግሞም ተማሪ ተማሪን አይገድልም። ኦሮሞ ተማሪዎች  ልጄን አልገደሉትም። ልጄን የገደሉብኝ አማራና ኦሮሞን ለማጋጨት የሚፈልጉ ሃይሎች ናቸው። የምጠረጥረውም መንግስትን ነው።” ሲል ሴራውን ማጋለጡ የወያኔን ፍላጎት በትክክል እንድንገነዘብ ያስቻለ አንድ ማሳያ ሆኖ አልፎአል።

የኦሮሚያ አመፅ ወደ አማራና ኦሮሞ ግጭት እንዲለወጥ ያደረጉት ሙከራ እስካሁን አልተሳካላቸውም። የመሆን እድል ግን አለው። ለዚህም ባለማወቅና በተዘዋዋሪ ወያኔን የሚጠቅም ተግባር የሚፈፅሙ ወገኖች አስተዋፅኦ አብይ ድርሻ አለው።
             እንደምንሰማው የኦሮሞ ወጣቶች (Qeerroo) አምስቱንም የፊንፊኔ በሮች የመዝጋት ልምምድ ሲያደርጉ ሰንብተዋል። በየአመቱ ሲካሄዱ የከረሙት የእሬቻ በአላት እንደ ኦሮሞ ህዝብ ኮንፈረንስ የሚታሰቡ ነበሩ። ሚሊዮናት ከተገኙበት ካለፈው አመት የቢሾፍቱ ኮንፈረንስ በሁዋላ የኦሮሞ ወጣቶች ላለፉት ሁለት ወራት የተግባር ስልጠና ላይ ቆይተዋል። ከጥር አጋማሽ ጀምሮ በሃረርጌ ያየነው ሜንጫ (ማሽላ መቁረጫ ረጅም ማጭድ)፣ እንዲሁም የሰማነው መፈክር (ባዶ እጅ መውጣት አበቃ!) የስልጠናው ማብቃት ምልክት ይመስላል። በርግጥም አመፁ ቀጥሎአል። ይህን መጣጥፍ እየከተብኩ ሳለ እንኳ የኦሮሞ ወጣቶች በምእራብ ሃረርጌ፣ በቦርደዴ፣ በመኤሶ፣ በአሰቦትና በምእራብ ሸዋ ከፌደራል ፖሊስ ጋር በጠመንጃ እየተፋለሙ ነው። በምስራቅ ወለጋና በሆሮ ጉዱሩ የተቃውሞ ሰልፎች ቀጥለዋል። ወያኔ እንደሚመኘው አመፁ ሊቆም እንደማይችል ርግጠኛ ወደመሆን ደረጃ ላይ ተደርሶአል። ወያኔ በህዝባዊው ማእበል ከመጠረጉ በፊት በግልፅነት ቀርቦ ከሁሉም ተቃዋሚ ወገኖች ጋር ድርድር ማድረግ ይበጀዋል። ካልሆነ እንደ ደቡብ ሰዎች አባባል “እንኳን በገባበት ወጣ” ሊገጥመው ይችላል።
“ሞረሽ” ውጭ አገር በሚኖሩ አማሮች የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን፤ ኦሮሞ ወደ ስልጣን ከመጣ አማራ ለአደጋ ሊጋለጥ እንደሚችል እየገለፀ ነው። ወያኔም ከአፋቸው እየቀለበ፣ “ልክ ናችሁ። ‘ከሁለት ዛፍ ያጣ - እድለ ቢስ ጦጣ’ እንዳትሆኑ ተጠንቀቁ።” እያለ በእጅ አዙር ያሟሙቃል። ወያኔ የሞረሽን ስጋት ለጥቅሙ እያዋለው ነው። የአባይ ፀሃዬ ወቅታዊ የጦርነት ስልት የሞረሽ ደጋፊዎችን ከቄሮ (Qeerroo) ማላተም ይመስላል። ርግጥ ነው፤ በአብዛኛው የአንድነት ሃይሎች በሞረሽ መደራጀት ደስተኛ እንዳልሆኑ ይታወቃል። ድርጅቱ ሲመሰረት ከጥቂት በላይ የአማራ ልሂቃን መቃወማቸው ትዝ ይለኛል። በርግጥ ሞረሽ በተለይ አማራው ላይ የሚካሄደውን ጥቃት ለመቋቋም መመስረቱን ይገልፃል። በቅርቡ የሞረሽ ደጋፊ መሆኑን የገለፀ ሰው ፓልቶክ ላይ እንዲህ አለ፣

“እየሩሳሌም ማለት ‘አየሩ ሰላም’ ማለት ነው። ዳረሰላም ደግሞ ‘የሰላም ዳር’ ማለት ነው። ይህም አባቶቻችን እስከ እስራኤልና ታንዛንያ ዘልቀው ያስተዳድሩ እንደነበር ምልክት ነው።”

ይህ አባባል ታሪካዊ ማስረጃ ቢኖረው እንኳ በዚህ ወቅት ምን ይጠቅማል? ወያኔ ጣና ሃይቅን፣ ራስዳሸን ተራራን እና የዋልድባ ገዳም ወንዞችን ከአማራ ይዞታ ለማላቀቅ ሌት ተቀን ሲደክም አቶ እንቶኔ  ስለ ዳረሰላም ያወራል። “ዳረሰላም የኛ ነበር” ከሚለው ኩራት “ጣና ሃይቅ የኛ ነው” ወደሚል እንጉርጉሮ መውረድ መስፍን ወልደማርያም እንደሚሉት የቁልቁለት ጉዞ ነው። እንዲህ በመሆኑ ያሳዝናል። ድክመቱ የአማራ ህዝብ ሳይሆን የፖለቲከኞቹ ራእይ ማጣት ነው። ይህም ድክመት ወያኔ በስልጣን እንዲቆይ ሚዛን ጠብቆለታል።

የቤተ አማራን ድረገፅ ሳነብ ደግሞ ሌላ ቀልድ አገኘሁ። አንዱ ፀሃፊ፣ “መሬታችን ተቀምቶ ለሱዳን ሲሸጥ፤ ሌላው ቢቀር ጎንደር እንዴት ዝም ይላል?” ሲል ጠየቀ። አባባሉ ጎንደር በጀግንነቱ ከሌሎች ሁሉ የላቀ ነው ለማለት ይመስላል። የወያኔ አሽሟጣጭ ይህችን ከአፍ ቀልቦ፣ አፄ ቴዎድሮስ ትግሬ መሆኑን ነዛ። በአንድ ወገን ደግሞ አጤ ቴዎድሮስ ቅማንት መሆኑን የደራሲ ብርሃኑ ዘርይሁንን “የታንጉት ምስጢር” ዋቢ አደረገ። እንግዲህ አንዳንድ ስራፈቶች ስራ አገኙ ማለት ነው። “አማራ ተደፈርክ! ቴዎድሮስን ስትነጠቅ ምን ትጠብቃለህ? ከዚህ በላይ ምን ትሆናለህ? ክተት! አትነሳም እንዴ? ትግስትህ አያልቅም እንዴ?” የሚል እሪታ ጆሮአችንን ሊበሳ ደረሰ። ከቴዎድሮስ ትግሬ ሆኖ መገኘት ጋር በተያያዘ የተቆጣ ሌላ የሞረሽ ደጋፊም ትምክህቱ ነሽጦት በፈረስ ስም ተሸሽጎ ፃፈ፣

“…ዛሬ መሬታችንን እየቆረሱ የሚሸጡ ትግሬዎች፣ ትናንት ጎንደር ደጃፍ እየመጡ የሚሰግዱልን ለማኞች ነበሩ። ምልክቱም ጎንደር የሚገኘው ‘ትግሬ መጮሂያ’ አምባ ነው።”  

ርግጥ ነው በጥንት ዘመን ጎንደር ደጃፍ ላይ “ትግሬ መጮሂያ” የሚባል አምባ ነበር። ትግሬዎች ለልመና ሳይሆን ለአቤቱታ ጎንደር ይሄዱ ነበር። አባባሉ ትግሬን የማናናቂያ መገለጫ ሆኖ ቆይቶአል። ይሄ ‘ትግሬ መጮሂያ’ የተባለው አምባ ግን ዛሬ ወደ ‘ትግሬ መዝናኛ’ እንደተለወጠ ፀሃፊው አልሰማም። በግልባጩ የዋልድባ ገዳም አምባ “አማራ መጮሂያ” የሚል ቅፅል ስም ተሰጥቶታል። በመለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት አባይ ፀሃዬ ስኳር ምርት ላይ ሲሾም እንደተጣለ ተቆጥሮ ነበር። በስኳር ምርት ስም የአፋርና የዋልድባን ዙሪያ መሬትና ወንዞች የመቆጣጠር ምስጢራዊ ተልእኮ ይዞ መዝመቱን የተረዳ አልነበረም። የወያኔ የመጨረሻው አንጓ አልተገመተም ነበር።

ዞረም ቀረ አባይ ፀሃዬ ገንፍሎ የመጣበትን ህዝባዊ አመፅ በማዳፈን ወደ ዋና ግቡ መጓዝ የሚችለው በርግጥም ያልነቃውን አማራና ኦሮሞ በመጠቀም ነው። በዚህ ወቅት ሌላ ዘዴ የለውም። በመሳሪያ ሃይል ማፈን አይችልም። ጨዋታው የጭንቅላት ጨዋታ ነው። ለበጎም ተጠቀመበት ለክፉ አባይ አደገኛ ጭንቅላት አለው። እና ወያኔ እንደ ሞረሽ ያሉ ቡድኖችን እንዴት ስራ ብዙ እንደሚያደርጋቸው ያውቃል። በቀላሉ ቦይ ቆፍሮ ወደ ፈለገው መንገድ ይመራቸዋል። ለዚህ አባባሌ አንድ አብነት መጥቀስ ይቻላል…   

…ከአመታት በፊት የወያኔ መንግስት ባካሄደው የህዝብ ቆጠራ የአማራ ህዝብ ቁጥር ከሚታወቀው ወይም ከሚገመተው መቀነሱ ታውቆ ነበር። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የሞረሽ ሰዎች ዛሬም ድረስ እሪታቸውን ያሰማሉ። በወቅቱ የአማራ ህዝብ ቁጥር ሊቀንስ የቻለበትን ዋና ምክንያት ለመደበቅ ሲባል ወያኔ የፈጠራ ምክንያት ራሱ አሾልኮ አወጣ። ይህም እንዲህ የሚል ነበር፣

 “ወያኔ ሆን ብሎ የአማራን ህዝብ በHIV ኤድስ እያጠቃ ነው። በባህርዳር እና በዙሪያው ገጠር የአማራ ሴቶች እንዳይወልዱ መካን የሚያደርግ መርፌ በመወጋታቸው የአማራ ህዝብ ቁጥር እየቀነሰ ነው።”

ይህ ክስ ዛሬም ድረስ ይነሳል። ይህንን መረጃ በመደጋገም የአማራን ህዝብ ለማነሳሳት እየተሞከረ ነው። ወያኔ ግን ክሱን አስተባብሎ አያውቅም። የአማራ ህዝብም በዚህ መረጃ ተቆጥቶ እስካሁን አልተነሳም። በመሰረቱ ወያኔ እንዲህ ያለ ድርጊት መፈፀሙ ተረጋግጦ ከሆነ፤ እናም ይህን ፈፅሞ ሳለ በስልጣን መቆየት ከቻለ፤ በዚህ የሚወቀሰው ወያኔ ሳይሆን ወንጀሉ ተፈፀመበት የተባለው ህዝብ ነው። በየትም አለም አንድ ህዝብ ከዚህ የከፋ በደል ሊፈፀምበት አይችልም። አንድ ህዝብ “እንዲህ ያለ በደል ተፈፅሞብሃል” እየተባለ ዝም ካለ ያ ህዝብ በድን ሆኖአል ወይም መረጃውን አላመነም ማለት ነው። እንደኔ ግምት መረጃው አልታመነም። ወያኔ በህዝብ ላይ በተጨባጭ እየፈፀመ ያለው አንድ ሺህ አንድ ክፉ ድርጊቶች እያሉ ወደ ፈጠራ ክስ መግባት ለምን አስፈለገ? በፈጠራ ክስ ሲወነጀል ወያኔ በጣም ተጠቃሚ ይሆናል። በዚህ ወቅት የኦሮሞ ህዝብ አመፅ በተሳካ ሁኔታ መቀጠል የቻለው ተጨባጭነት ያለው ጥያቄ በማንሳቱ ይመስለኛል።

ከተነሳ ላይቀር ግን የአማራ ህዝብ ቁጥር ሊቀንስ የቻለባቸው አንዳንድ መረጃዎች አሉ።  

እንደምናውቀው ባለፉት ስርአቶች (በተለይ በቅድመ ደርግ) አማራ መሆን ጥቅም እና ከለላ ያስገኝ ነበር። በዚህ ምክንያት “አማራ” ሳይሆኑ በሚሞሉ ቅፆች ላይ “አማራ” ብለው የሚሞሉ ዜጎች ነበሩ። ጄኔራል ታደሰ ብሩን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። አክሊሉ ሃብተወልድ ስለ ጄኔራሉ ማንነት የተሳሳተውና የኦሮሞን ህዝብ የሚጎዳ አሳብ የተናገረው የተሞላውን ቅፅ አይቶ ጄኔራሉ መንዜ ናቸው ብሎ በማመኑ ነበር። ከደርግ ውድቀት በሁዋላ አማራ በመሆን የሚገኝ ጥቅምና ከለላ በማብቃቱ ብዙዎች ወደ ማንነታቸው ተመልሰዋል። ይህ የአማራን ህዝብ ቁጥር ከቀነሱት ምክንያቶች አንዱ ነው። ተጨማሪ ምክንያትም ይኖራል። አገው ቀደም ሲል አማራ ይባል ነበር። በዚህ ዘመን ከአማራነቱ ተቀንሶአል። ለአብነት ተርጓሚና ጋዜጠኛ ማሞ ውድነህ፣ ድምፃዊቷ እጅጋየሁ ሽባባው (ጂጂ) ቀደም ሲል አማራ ነበሩ፤ በወያኔ ስርአት ግን አገው ተብለው ይታወቃሉ። አማራን የወከሉ በርካታ የብአዴን አመራር አባላት ቅፅ ሲሞሉ አገው ናቸው። ለመጥቀስ ያህል ደመቀ መኮንን፣ ጄኔራል አበባው ታደሰ፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ ታደሰ ጥንቅሹ፣ የበረከት ስምኦን ሚስት አሰፉ ፈንቴ አንደ  አማራ ቢታወቁም አገው ናቸው። የአማራን ቁጥር በመቀነስ ረገድ የፈላሻ መሄድም አስተዋፅኦ አድርጎአል። ለአብነት ጋዜጠኞቹ ዜናነህ መኮንን እና አለምነህ ዋሴ በቀድሞ ጊዜ አማራ ነበሩ። አሁን ግን አማራነታቸውን በመተው ቤተ-እስራኤል መሆናቸውን ሰምተናል። የአማራ ቁጥር ወደፊትም እየቀነሰ ይሄዳል። በጣና ሃይቅ ዙሪያ የሰፈሩት ቅማንት እና ዋታ (ወይጦ) እስካሁን በአማራነት የተመዘገቡ ነበሩ። ዳሞትና አውራምባም አማራ አይደሉም እየተባለ ነው። በወያኔ አካሄድ እነዚህም ከቤተ አማራነት እንዲሰናበቱ እየተገፉ ነው። እንዲህ ያሉ መረጃዎችን ከማወቅ ይልቅ፣ “ወያኔ አማራን በኤድስ ፈጀው” የሚለውን ወያኔ ራሱ የለቀቀውን ፕሮፓጋንዳ መልሶ ማስተጋባት ከቀልድ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም። በማይታመነው በዚህ ክስ ተጠቃሚው ወያኔ ነው።

ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት የኦሮሞ ህዝብ አመፁን አጠናክሮ ቀጥሎ ብቻውን የወያኔን ስርአት ለማስወገድ ከበቃ ለሌላው ወገን ለፀፀት የሚያበቃ ታሪካዊ ስህተት ይሆንበታል። በአብሮ መኖር ሂደት ሌሎች የሚሉትን መስማት ቀዳሚ ጉዳይ ነው። የኦሮሚያን አመፅ ሌሎች ኢትዮጵያውያንም እንዲሳተፉበት ሲጠየቁ፤ ለነገ አብሮነት በማሰብ እንጂ የኦሮሞ ህዝብ ብቻውን ወያኔን ማንበርከክ አይችልም ከሚል አልነበረም። ይህን አብሮ የመታገል ጥያቄ በተሳሳተ መንገድ የተገነዘቡ ወገኖች ወያኔን ስልጣን ላይ በማቆየቱ ረገድ የማይናቅ ድርሻ እያበረከቱ ነው። የቅርብ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኦሮሚያ ላይ እድሮች መፍረስ ጀምረዋል። ከአማራ ህብረተሰብ ጋር ለረጅም ጊዜ አብሮ የመኖር ልምድ የነበራቸው የኦሮሞ አዛውንቶች እየተቀየሙ መሆኑን ተረድቻለሁ። ልጆቻቸው ከአፋኙ ስርአት ጋር እየተፋለሙ ሲወድቁ ሌሎች ዳር ቆመው መመልከታቸውን በመታዘብ ከእነዚህ ወገኖች ጋር በአንድ እድር መቆየት የህሊና ቁስል እንደሆነባቸው በኦሮሞ ማህበራዊ ድረገፆች እየተነገረ ነው። አደገኛ አዝማሚያ ይመስለኛል። ወያኔ የሚፈልገው መንገድ ይመስለኛል። ለነገው አብሮ መኖር እንቅፋት የሚሆን ይመስለኛል።

 መረራ ጉዲና 2014 ላይ ባሳተመው መፅሃፍ ከጠቆማቸው ይሆናል (Scenario) አንዱ ኢትዮጵያ በማያቋርጥ ቀውስ ተንጣና በስብሳ ወደ መበታትን ልታመራ እንደምትችል ነበር። በተለይም የአማራ ልሂቃን ዋና በሽታ የቀድሞይቱን ኢትዮጵያ እንደነበረች ለማስቀጠል መፈለጋቸው መሆኑን በግልፅ ቋንቋ አስቀምጦታል። የአማራ ልሂቃን የኢትዮጵያዊነትን የምስክር ወረቀት ሰጭና ከልካይ አድርገው ራሳቸውን መሰየማቸው በጋራ የመኖር ተስፋውን እንደጎዳው መረራ ይገልፃል። በአባይ ፀሃዬ እየተመሩ ያሉት የትግራይ ልሂቃን በአንፃሩ “ስልጣን ወይም ሞት” በሚል እብደት ላይ መሆናቸውን መረራ አስምሮበታል። በዚህ ወቅት አብዛኛው የኦሮሞ ልሂቃን ሉአላዊት ኦሮሚያን ማየት እንደሚመኙም አልሸሸገም። ልሂቃኑ አንዱ ሌላውን ከማይሰማበት የደንቆሮዎች ውይይት (Diallogue of a deaf) ራሳቸውን ማላቀቅ ካልቻሉ መፍትሄው እየራቀ እንደሚሄድም ገልፆአል።

ከመረራ የሰላ ትችት አንፃር የሞረሽ ደጋፊዎችን ስንገመግም፤ የQeerrooን መንገድም ስንታዘብ ከፊታችን የመቻቻል ተስፋ አለ ብለን ለመናገር አንደፍርም። ተስፋ ማድረግ ግን ይገባል። ተስፋ ከሰማይ እንዲወርድ ሳይሆን ሌላው ወገን የሚፈልገውን ለመቀበል ከግማሽ መንገድ በላይ መጓዝ ያስፈልጋል። ይህም መንገድ የእርቅ መንገድ ነው። የማታለል ሳይሆን፣ የጥሎ ማለፍ ሳይሆን በሃቅ ላይ የተመሰረተ የእርቅና የመቻቻል መንገድ ነው። የአማራ ልሂቃን ቢያንስ ኦሮሚያን እንደ ክልል በማወቅ የመቀራረቡን መንገድ መክፈት ይጠበቅባቸዋል። ወያኔም ከሰመመኑ እንዲነቃ ይጠበቃል። አዲሳባ ላይ የአህዮችን መብት የሚያስከብር ቢሮ እንዲከፈት የፈቀደ መንግስት፤ በዚያው አመት የመጫና ቱለማ ማህበርን መዝጋቱ ለህዝቦች መብት መከበር ሲል የተሰዋውን የህወሃት ታጋይ መካድ ነው።

 በቀድሞ ዘመን ኦሮሞን የሚንቁ ወገኖች እንደነበሩ እናውቃለን። ሳይቸግራቸው ንቀቱን የወረሱ ወጎኖች ዛሬም አሉ። እነዚህ ወገኖች ሳያውቁት ለአባይ ፀሃዬ ጦርነት ድጋፋቸውን እየሰጡ ነው። ተጨባጩን እውነት መረዳት ይገባል። አዲሱ የኦሮሞ ትውልድ የንቀቱን ዘመን በታሪክ እንጂ በአካል አያውቀውም። ዛሬ እንደ ፈነዳ ወንዝ ተቆጥተው ወያኔን እያንቀጠቀጡ ያሉ ወጣቶች ከ15ኛው ክፍለዘመን ኦሮሞዎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። የኦሮሞ ወጣት ፈረሰኞች ዛሬ በሃረርጌና በአመያ፣ በከረዩና በቦረና፣ በሌቃዱለቻና በሆሮጉዱሩ፣ በአምቦና በሰላሌ እንዲሁም በሌሎች የኦሮሚያ ክፍለሃገሮች ዳግም ታይተዋል። ኦሮሞነትና ኦሮሙማን፤ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጋር አስታርቆ ለመጓዝ መካከሉ ላይ መላ መፈለግ እንጂ የኦሮሚያን ህልውና መካድ መፍትሄ አያመጣም። አይናችን እያየ ዘመን ተለውጦአል። አንድ አዲስ ትውልድ እድሜው ለፈረስ ግልቢያ ደርሶአል። ሃጎስ ወይም ጌታቸው የተባሉ ስርአቶች ዛሬም እንደ ትላንት ቶለሳን በፈረቃ ለመግዛት የሚያልሙ ከሆነ ምኞታቸው ከህልም አያልፍም። ኢትዮጵያ በተባለችው አገር ላይ በተለይ የኦሮሞና የአማራ ህብረተሰብ ተከባብሮ በአንድነት መኖር የሚችለው መራራም ቢሆኑ እውነታዎችንና የህዝቡን ጥያቄዎች መቀበልና መገንዘብ  ሲቻል፤ በፈረቃ እያጋጩት ለመዝለቅ የሚያልሙ ወገኖችን ተንኮል በመረዳት ማክሸፍ ሲቻል ብቻ ይመስለኛል።

በመጨረሻ ይህችን መጣጥፍ መሰንዘሬ የኢትዮጵያ ጉዳይ፤ በጥቅሉ ደግሞ የአፍሪቃ ቀንድ ህዝቦች መጪ እድል ስለሚያሳስበኝ ነው። ርግጥ ነው፤ እንዲህ በግልፅነት መፃፍ ከስድብኤል ኮሌጅ ለተመረቁ ተሳዳቢዎች የስድብ ውርጅብኝ ያጋልጣል። ቢሆንም በአካባቢያችን አንዱ ስለሌላው “አያገባኝም” ሊል አይችልም። ወደድንም ጠላንም የማደግም ሆነ የመውደቅ እድላችን የተሳሰረ ነው። ችግሮቻችንን በጋራ ለመፍታት መሞከር ብቸኛው ወይም የተሻለው ምርጫ ነው። በአንዱ ውድቀት ሌላው አትራፊ ሊሆን አይችልም። ጉዳያችን ለየቅል ቢሆን፣ “ምናገባኝ” ማለት በተቻለ። “ምናገባኝ” ማለት አለመቻል በእውነቱ አለመታደል ነው…

 Gadaa Ghbreab: www.tgindex.blogspot.com  ttgebreab@gmail.com  Jan. 28  2016         

13 comments:

Anonymous said...


Tesfaye: you ara always among the true speakers!

Anonymous said...

So Cool Gadaa (Tesfaye). I honour your incredible effort to tell the truth to all concerned persons in Ethiopia. Keep on!

Meskerem said...

በነዚሁ ምስኪን ህዝቦች ( ማለትም “አማራ” እና “ኦሮሞዎች”) መካከል መርዝን ከረጩ በኋላ በመፀፀት ይቅርታ እንኳን ሳይጠየቅበት ያገባኛል!? እረ በህግ!

Anonymous said...

የካብ ዉስጥ እባብ!! እባቦች አመች ጊዜያቸዉን ጠብቀዉ ይናደፋሉ!! አንተም እንደዛዉ ጊዜ ጠብቀህ መካሪና አዛኝ መስለህ ለኦሮሞ ተቆርቋሪና ኦሮሞ መስለህ የትግራዋይ ዝቃጭ አስተሳሰብህንና ጠባብነትህን ትቀባዋለህ!! አይ! አረብ ለካ አረቦች ናችሁ!!

obsa.ambo said...

Gadaa..........Aboo nama ajaa'ibaatim ati! Galatoomi!..........እግዜር ሁሌም እዉነትን ታሰብክህ!! Wow!

Anonymous said...

Who are you? to give us recommendations? give credit The late Prime Minister, Meles Zenawi when on saying either we swim together or sink together
kiss your wedi afewerki's ass

Anonymous said...

Aboo yimachih!!!!! Gadaa.

Unknown said...

Some people may insult you if they can't manage to bit or shoot you while you are exposing the truth they don't want to told! You are lucky in that you are out of their arm!

Unknown said...

የሻቢያ ቡችላ
🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹🇪🇹
Leave us alone

Unknown said...

Great article
You are always at the heart of Oromo people. I have read all what you have written starting from Burka zimta. God belss you and we love you.

Anonymous said...

we realy respict you Mr. Gada your article based on the truth the oromo plp needs to acssept reality and also diallogue.

Anonymous said...

zemenu yeweldew Denke xehafi Ewenten lemnager yemifera. sewoch alafi nachew serachew gen hulem yenageral Ende Geda ayenet xehafiwoch bezu yasfelgunal Ewenten tenagrew beyalfum enkwan serachew gen hulgezem ke mekaber belay new.Geda Ewentun bexhume yegelxal tesadabiyoch menentachewen bexhufachew yegelxalu.keep it up Geda.

Unknown said...

Credible article,based on reality which can cteate awareness for ethiopians to narrowing or resolving their differences