Friday, January 16, 2015

የብእር ጦርነት



ፊስቡክ ላይ በስሜ አካውንት ከፍተው፣ አሉባልታና ጥላቻን እየፃፉ በኔ ስም የሚያሰራጩ የሳይበር አርበኞች ተከስተዋል። ከጃዋር መሃመድ ጋር በዚሁ ጉዳይ በስልክ ተነጋግረንበት ነበር። ይህን የሚፅፉት ከወያኔ ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው የሚችሉ ኦሮሞዎች መሆናቸውን ጠቁሞኛል። ይህ የሚያስገነዝበኝ ሰዎቹ አሳቦችን በአሳብ መመከት አለመቻላቸውን ነው።

ባለፈው ሳምንት “የሌንጮ ለታ መንገድ” በሚል ርእስ አንድ መጣጥፍ ፅፌ ነበር። ምስራቅ የሚል የብእር ስም የምትጠቀም ሴት ኢትዮጵያን ሪቪው ላይ በኔ ስም አካውንት ከፍታ፣ የኔን ፅሁፍ ትለጥፋለች። እናም የራሷን ስድብ ሞነጫጭራ ስታበቃ፣ የሌሎችን አስተያየት ትደመስሳለች። የኔን ፅሁፍ ኢትዮጵያን ሪቪው ላይ ለመለጠፍ በኔ ስም አካውንት መክፈት ለምን እንዳስፈለጋት አልገባኝም።

በመሰረቱ እኔ ብሎግ አለኝ። www.tgindex.blogspot.com ይባላል። አሳቤን በዚህ ብሎግ ላይ እፅፋለሁ። ሌላ ቦታ መሄድ አያስፈልገኝም።

የሚጠሉኝ ሰዎች ፕሮፓጋንዳ ሲጨመቅ፣ “የሻእቢያ ሰላይ”፣ “እባብ”፣ “ኦሮሞና አማራን በማጋጨት ኢትዮጵያን የመበታተን አላማ ያለህ ሰይጣን።”፣ “ኤርትራዊ ስለሆንክ ስለኢትዮጵያ አያገባህም።” የሚል ነው። ከዚህ የተለየ ነጥብ የላቸውም። እነዚህ ሰዎች ይህን መሰል ርግማን ያወረዱበት ሰው የሚፅፈውን ፅሁፍ እየተከታተሉ ማንበባቸው ከልብ ያስቃል። ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚፃፍን ፅሁፍ በፍፁም ማንበብ ያለበት አይመስለኝም። እውነቱ ግን የተለየ ነው። ኢትዮጵያን የመበታተን አላማ እንደሌለኝ በልባቸው ያውቃሉ።

ለነገሩ ኢትዮጵያ በአንድ ደራሲ ፅሁፍ ልትናጋ ትችላለች ብሎ ማሰብ ራሱ ቀልድ ነው። ወይም በተዘዋዋሪ አሳብን የማፈን አዝማሚያ ነው። “ኦሮሞና አማራን ለማጋጨት” የሚለውን አባባል ኦሮሞዎች ተጠቅመውበት አያውቁም። የአንድ ወገን ሰዎች ብቻ የሚጠቀሙበት ከሆነ የአባባሉን ምክንያት በቀላሉ መረዳት ይቻላል። ‘ስለ ኢትዮጵያ ምናገባህ?’ የሚሉኝ ሰዎች ስለ ኤርትራ በመዝፈን የታወቁ ናቸው። ነጋ ጠባ ሌላ አጀንዳ የላቸውም። ለሚያጋጥማቸው ችግር ሁሉ ሻእቢያና ኤርትራን ተጠያቂ ያደርጋሉ። ዞረም ቀረ ባለፉት 20 አመታት በኢትዮጵያውያን ፀሃፊዎች ስለ ኤርትራ የተፃፉ መፅሃፍት 28 ሲደርሱ፤ “ከኤርትራውያን” በኩል ስለ ኢትዮጵያ የሚፅፈው አንድ ደራሲ ብቻ ነው።

No comments: